የኢትዮጵያ መንግስት እዳ 62.5 ቢሊዮን ዶላር መድረሱ ተገለፀ


የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ማህበር ዛሬ ባወጣው ሪፖርት አገሪቱ ከፍተኛ የብድር ጫና ውስጥ መግባቷን አስታውቆ ለውጭ ገበያ ከሚቀርበው የሚገኘው ገንዘብና መንግስት የሚሰበስበው ገቢ ለእዳ መክፈያ እየዋለ መሆኑን አስረድቷል፡፡ ማህበሩ በሪፖርቱ ‹‹ኢትዮጵያ በአንድ ወቅት ከአለም ፈጣን ኢኮኖሚ ካስመዘገቡ አገራት ተርታ ተሰልፋ ነበር›› ካለ በኋላ ካለፈው 10 አመት ወዲህ እድገቷ ማሽቆልቆሉን አስታውቋል፡፡ እየጨመረ የመጣው የዋጋ ንረት የዜጎችን ኑሮ ስጋት ውስጥ መክተቱን አስረድቶም ከዚህ መውጫ ያላቸውን ምክረ ሀሳቦች ለግሷል፡፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ማህበር አሁን ያለው የኢትዮጵያ እዳ 62.5 ቢሊዮን ዶላር የገለፀ ሲሆን ከወራት በፊት ይፋ የሆነው አንድ መረጃ ደግሞ እዳው 56.7 ቢሊዮን ዶላር መሆኑን አስታውቆ ነበር፡፡  በተመድ አማካኝነት ይፋ የሆነው ይህኛው መረጃ እንዳለው የኢትዮጵያ እዳ በተለያዩ መንገዶች የሚገለፅ ነው፡፡ ለምሳሌ ከአለም አቀፍና አህጉራዊ ድርጅቶች የተበደረችው መጠን 24 ቢሊዮን ዶላር ይደርሳል፡፡ ከተለያዩ አገራት የተበደረችው ደግሞ 9.5 ቢሊዮን እንደሚሆንና ከግለሰቦች ያለባት ብድር 17 ቢሊዮን ዶላር መሆኑን አስረድቷል፡፡

Source: VOA Amharic