ለሀገር አቀፍ የምክክር ጉባኤ ከአማራ ክልል የተሰበሰቡ አጀንዳዎች


ከይር ዜና:- የአማራ ክልል በመጪው ሀገር አቀፍ የምክክር ጉባኤ ላይ እንዲቀርቡ ካስመዘገባቸው አጀንዳዎች መካከል፤ የህገ መንግስት ማሻሻያ፣ የማንነት እና የወሰን ጥያቄዎች፣ የፍትሃዊ የሃብት ተጠቃሚነት እና የስልጣን ክፍፍል ጉዳዮች ይገኙበታል። ከአማራ ክልል ውጭ የሚኖሩ የክልሉ ተወላጆች ዕጣ ፈንታ፣ የአማራ ህዝብ ቆጠራ በትክክል እንዲካሄድ እና አዲስ አበባ ራሷን ችላ ክልል እንድትሆን የሚሉ ጉዳዮችም በአጀንዳነት ተመዝግበዋል።

እነዚህን ጨምሮ በአጠቃላይ 13 አጀንዳዎችን አጠናቅረው ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነሮች በዛሬው ዕለት ያስረከቡት፤ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችን እና ባለድርሻ አካላትን የወከሉ 25 ግለሰቦች ናቸው። የአጀንዳ ርክክቡ የተካሄደው፤ በአማራ ክልል ደረጃ ለአንድ ሳምንት ያህል በባህርዳር ከተማ ሲካሄድ የቆየው የምክክር መድረክ መጠናቀቁን ተከትሎ ነው። 

በዚህ የምክክር መድረክ በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ላይ እንዲሳተፉ የተመረጡ 4,500 የማህበረሰብ ወኪሎችን ጨምሮ በአጠቃላይ ስድስት ሺህ ሰዎች ተሳትፈውበታል። ኮሚሽኑ ከተረከባቸው የአማራ ክልል አጀንዳዎች መካከል “የህግ የበላይነት፣ የአገር ሉዓላዊነት እና የውጭ ግንኙነትን” የተመለከቱ ጉዳዮች አጀንዳውን ካጠናቀሩ ተወካዮች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ መሐመድ ኢብራሂም ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

ምንጭ፡- ኢትዮጵያ ኢንሳይደር