በመዲናዋ የሚገኙ የመንግሥት ሠራተኞችን የቤት ባለቤት ለማድረግ ስምምነት ተፈረመ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 41 ሺህ የመንግስት ሰራተኞችን የመኖሪያ ቤት ባለቤት የሚያደርግ የ25/75 ቤቶች ልማት ፕሮጀክት በጋራ ለማልማት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል። ይህ ስምምነት በተለይም ለመምህራን ቅድሚያ እንደሚሰጥ ተገልጿል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቤቶች ልማት አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ቅድስት ወልደ ጊዮርጊስ እንደገለጹት፤ ስምምነቱ ቤት የሌላቸውን የመንግስት ሰራተኞችን ችግር ለመቅረፍ ያለመ ነው ተብሏል።

የመንግስት ሰራተኞች 25 በመቶ የቤቱን ዋጋ እንዲቆጥቡ የሚጠበቅ ሲሆን፤ ቀሪው 75 በመቶ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብድር እንደሚሸፈን ተጠቁሟል። የብድሩ ጊዜ ለ20 ዓመታት የሚከፈል ሲሆን፣ በከተማዋ የሚገኙ 41 ሺህ የመንግስት ሰራተኞችን ተጠቃሚ ያደርጋል። ከፕሮጀክቱ የአዲስ አበባ መምህራን ቅድሚያ ተጠቃሚ እንደሚሆኑም ወይዘሮ ቅድስት አክለዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ እንደተናገሩት ባንኩ ለዚህ ፕሮጀክት 120 ቢሊዮን ብር ብድር ለማቅረብ አቅዷል። የብድሩ ወለድ 14 በመቶ ሲሆን፤ ለ20 ዓመት የሚከፈል መሆኑን አስረድተዋል።