ዜናው በተወሰነ ደረጃ የመንግስትን የታሰበበት የፓሊሲ ፍላጎት(deliberate policy intention) ማሳያ ይሁን ወይም በአጋጣሚ የተወሰነ ውሳኔ መሆን አለመሆኑ ወደፊት የምናየው ሆኖ ዝርዝሩን ግን በደንብ ከመረመርነው በርካታ አስቸጋሪ ጉዳዮች እንዳሉት መረዳት ይቻላል።
አሁን ካለው እና ወደፊት ከሚጨምረው የግንባታ ዋጋ መናር ጋር ተያይዞ እስኪ እንዴው አንድ ትዳር ያለውና ሁለት ወይም ሦስት ልጆች ያሉት የመንግስት ሰራተኛ ሁለት መኝታ ቤት ያለው የጋራ መኖሪያ ቤት ይፈልጋል ብለን እንውሰድ። ፕሮግራሙ ወደ ተግባር ሲገባ የዚህ ቤት ዋጋ በትንሹ 5 ሚለዮን ብር ግምታዊ ዋጋ ይኖረዋል ብለን እናስብ።
የመንግስት ሰራተኛው አሁን ያለው ደመወዝ ተጣርቶ በወር 12,000 ብር ይደርሰዋል ብለን ሰፋ ያለ ግምት እንውሰድ። በተመሳሳይ የትዳር አጋሩም ተቀራራቢ የሆነ ወርሃዊ ገቢ አላት ብለን እናስብ። ይህ ቤተሰብ በወር 24,ዐዐዐ ብር የተጣራ ገቢ አለው እንበል።
ስለዚህ በዚህ የቤት ልማት ፕሮግራም ላይ ለመሳተፍ ከፈለገ በመጀመሪያ 25 ከመቶውን መቆጠብ አለበት። የ5 ሚለዮን 25 በመቶው 1.25 ሚለዮን ብሩን ለመቆጠብ እንዴት እንደሚችል እንይ። ለምሳሌ ቤተሰቡ በአንዳቸው ደመወዝ በተዓምር እየኖሩ የአንዳቸውን የወር ደመወዝ በሙሉ 12,000 ብር ይቆጥቡ። ስለዚህ በአመት 12,000*12=144,000 ብር ይቆጥባል ማለት ነው። ስለዚህ 25 በመቶውን ለመቆጠብ 8.3 ዓመት ይፈጅበታል።
ከስምንት አመት በኋላ ደመዎዙ 20,000 ብር ይደርሳል ብለን እናስብ እና ለቤቱ የሚያስፈልገው 75 በመቶ ፋይናንስ ከንግድ ባንክ ተገኝቶ ተገነባ እና ተሰጠው። ብድሩ 3.75 ሚለዮን ብር ሲሆን አሁን ባለው የንግድ ባንክ ዝቅተኛ ወለድ በ16% ለ20 ዓመት ሲከፍል ወርሃው የባንክ ተመላሹ በትንሹ 48,693.95 ብር ይሆናል ማለት ነው።
ስለዚህ የዚህ የመንግስት ሰራተኛ ደሞዝ ለ20 ዓመት ሙሉ ሙሉ ደሞዙን ለሞርጌጅ እየከፈለ በተረከበው ቤት እንዲኖርበት ከፈለግን ቢያንስ ደመዎዙን ወደ 48,693.95 ብር ማሳደግ አለብን ማለት ነው።
የገንዘብ ሚኒስቴር በዚህ ወር መጨረሻ ላይ የ2018 ዓ/ም ረቂቅ በጀት ለፓርላማ ሲያቀርብ የመንግስት ሰራተኛውን የተጣራ አማካይ ደመዎዝ ቢያንስ 48,693.95 ብር አድርጎ የበጀት ጥያቄ እንደሚያቀርብ። ይሄ ብር በዶላር ሲሆን ምን አለው? ያው 374.5 ዶላር ብቻ ነው። ምስራቅ አፍሪካ ከእኛ በታች ጥቅል አመታዊ ምርትና የነፍስ ወከፍ ገቢ ያላቸው አገራት እንኳን ወርሃዊ የመንግስት ሰራተኛ (ለምሳሌ ለዶክተሮች እና ነርሶች) ደመወዝ ከዚህ በላይ እንደሚከፍሉ ከታች ከተያያዘው ግራፍ ላይ መረዳት ይቻላል።
ከብዙ የአፍሪካ ሀገራት የተሻለ አድገናል ከተባለ፣ ከምስራቅ አፍሪቃ በጥቅል አገራዊ ምርት አንደኛ ከሆን፣ በነፍስ ወከፍ ገቢያችንም ከተሻሻለ ቢያንስ የመንግስት ሰራተኛው ደመወዝ ከጎረቤቶቻችን የተቀራረበ መደረግ አለበት። ያለበለዚያ ሆድን በጎመን ቢደልሉት ጉልበት ዳገት ላይ ይለግማል እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። የኢትዮጵያ ሀኪሞች እና መምህራን እንዲሁም የሌሎች የመንግስት ሰራተኞች ጥያቄ ግልጽ፣ ቀጥተኛ እና የዳቦ ጥያቄ ነው። ሌላው ነገር ቢቀር ቢያንስ ለልጆቻችን ዳቦና ወተት የምናሟላበት መኖር የሚያስችል ደመዎዝ ይከፈለን ነው።
የወተት ጉዳይ ሲነሳ አንድ ሊትር ወተት አዲስ አበባ 110 ብር፣ ለወር 3300 ብር መድረሱ፣ አንድ እንቁላል 19 እስከ 21 ብር እንዲደርስ ያደረገው በ3 ተቃውሞ ፓርላማው ባለፈው ያጸደቀው በእንስሳት መኖ ላይ ጭምር ቫት እንዲጣል ያደረገው የተሻሻለው የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ነው። የዶሮም ሆነ የከብቶች መኖ ከእጥፍ በላይ እንዲጨምር በማድረግ ልጆች ወተትና እንቁላል እንኳን አግኝተው እንዳያድጉ እያደረገ ነው።
ከዚህ የከፋ አይምጣብን አይባል ነገር!
NB:- The opinions expressed herein are solely those of the author and do not necessarily represent the views of Keyir Media