ኖርዌይ፣ እንግሊዝ፣ ጣልያንና ፊንላንድ ካለባቸው የቆሻሻ መጣያ ቦታዎች እጥረት የተነሳ፤ በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ እየከፈሉ ቆሻሻዎችን ወደ ስዊድን ይልካሉ።
99.3 በመቶ የሚሆነውን የቤት ውስጥ ቆሻሻዋን ወደ ኤሌክትሪክ ኃይል የምትቀይረው ስዊድን፤ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ከሌሎች ሀገራትም ማስገባት ጀምራለች።
ስዊድን በተለያዩ ቦታዎች በተገነቡ 34 ቆሻሻን ወደ ኃይል የሚቀይሩ የማመንጫ ጣቢያዎቿ አማክኝነት፣ 99 በመቶ ከሀገር ውስጥ የሚሰበሰበውን ቆሻሻ ወደተለያዩ የሀይል ምንጮች መቀየር ችላለች።
ከዚህም በተጨማሪ ባሳለፍነው የፈረንጆች ዓመት 2024፤ ከተለያዩ ሀገራት ከ1.3 ሚሊዮን ቶን በላይ የሚሆን ቆሻሻ አስገብታ ከፍተኛ የኃይል ምንጭ ማግኘት ችላለች።
ስዊድን በነዚህ ቆሻሻን ወደ ኃይል በሚቀይሩ ማመንጫ ጣቢያዎች ተጠቅማ፤ 1.2 ሚሊዮን መኖሪያ ቤቶች የሙቀት ሓይል እንዲያገኙ የምታደርግ ሲሆን ከ800ሺህ በላይ የሚሆኑ መኖሪያ ቤቶችም የኤሌትሪክ አገልግሎት ማግኘት ችለዋል።
እንደ ‘ብሉ ኦሽን ስትራቴጂ’ ዘገባ ስዊድን ከራሷና ከተለያዩ ሀገራት በምታስገባው ቆሻሻ ከ1 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ የሚያወጣ ኃይል የምታመነጭ ሲሆን፤ በተጨማሪም ኖርዌይ፣ እንግሊዝ፣ ጣልያንና ፊንላንድ ቆሻሻቸውን ወደስዊድን በሚልኩበት ወቅት ከሚከፍሉት በየዓመቱ አንድ መቶ ሚሊዮን ዶላር ገቢ ታገኛለች።